በስምንት ወራት ውስጥ በህገ-ወጥ መልኩ ሲዘዋወር የተገኘ የተለያየ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮምሽኑ አስታውቋል፡፡የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፍንታ ለአሐዱ እንደተናገሩት ከተማ ውስጥ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዝብ ዝውወር ተበራክቷል፡፡
ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ከመረጃ መረብ ደህንነት አገልገሎት፣ ከፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን አደጋ ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡
በስምንት ወራት ውስጥም 3 ብሬን ጠመንጃ፣ 288 የተለያዩ ሸጉጦች፣ 100 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 5 ቦንቦች፤ 12 ሺ 796 የሸጉጥ ጥይት፣ እንዲሁም ሌሎች መሳሪያዎች በአጠቃላይ 13 ሺ 588 የጦር መሳሪያ ጥይቶች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በተሽከርካሪ ውስጥ በሚደረግ ፍተሻ በቦቲ ውስጥ እንዲሁም ህጻናት በሚጫወቱበት ቦታዎች ላይ የተጣሉ በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡በህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር ባለፉት 8 ወራት 586 መዝገብ የተከፈተ ሲሆን ፤ 701 ተከሳሶች በአጠቃላይ 686 ወንጀለኞች መያዛቸውን የተናገሩት ኮማንደር ፋሲካ 15 የሚሆኑት አንዳልተያዙ አስታውቀዋል፡፡
ፖሊስ ኮምሽኑ ያልተያዙትን ህገ-ወጦች ለመያዝ እየሰራ ሲሆን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለማስቆም ከሚመለከታቸው አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቀን 08/08/2013
አሐዱ ራድዮ 94.3