ታሕሳስ 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከበዓል ጋር በተያያዘ በከተማዋ የነዳጅ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ለአሐዱ ገልጿል፡፡
በቢሮው የገበያ መረጃ ጥናት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሰማ ጀማል፤ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በተለይ በዋዜማ አብዛኛው ሰው እንቅስቃሴ ስለሚያደርግና አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለውም አዲስ አበባ በየዕለቱ የሚያስፈልጋት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በከተማዋ ካሉ 125 ማደያዎች መካከል በ27ቱ ቤንዝል እንደሌላቸውና 7 የሚሆኑት በእድሳት ምክንያት ሥራ ያቆሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሊትር አቅርቦት ለከተማዉ እንዳለና ይህ ለከተማዋ በቂ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አክለውም "ህብረተሰቡ ማህበራዊ ሚዲያን በሚገባ እየተጠቀመበት አይደለም አንድ ቦታ ላይ 5 እና 6 መኪኖች ተሰልፈው ካየ የነዳጅ እጥረት ሊኖር ነው የሚል የተሳሳተ መረጃ እየታየ ነው" ብለዋል፡፡
ይህም የተሸከርካሪ ሰልፍ መነሻ አቅርቦት እጥረት ሳይሆን ስርጭቱ ጋር በተያያዘ ቤንዚን የጨረሱ እና ያዘዙ ማደያዎች በመኖራቸው መሆኑን አብራርተዋል።
አሽከርካሪዎች ይፋዊ የሆነውን የንግድ ቢሮ ትስስር ገጾች በማየት፤ ነዳጅ እና ቢንዝል ወዳለበት አካባቢ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።