ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ቦሉ ግዛት ግራንድ ካርታል በተሰኘ በሆቴል ውስጥ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 76 ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ 51 ሰዎች መጎዳታቸውን የግዛቲቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

በቦሉ ከተማ በእንጨት በተሸፈነው ባለ 12 ፎቅ ግራንድ ካርታል ሆቴል እሳቱ የተነሳው 234 ሰዎች በውስጡ በነበሩበት ወቅት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በአደጋው ከሞቱት ሰዎች መካከል ሁለቱ ከሕንፃው ወደ ውጭ ከዘለሉ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ተነግሯል።

Post image

እሳቱ በሆቴሉ ሬስቶራንት ውስጥ ሲቀሰቀስ ሕንጻውን በፍጥነት በማያያዙ የተደናገጡ እንግዶች፤ በመስኮት እየዘለሉ እንዲሄዱ ወይም ጊዜያዊ ገመድ ተጠቅመው እንዲያመልጡ መገደዳቸውን ዘገባዎች አመላክተዋል።

የቦሉ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልአዚዝ አይዲን እሳቱ በባለ 11 ወለሉ ሆቴል 4ኛ ፎቅ ላይ ከሌሊቱ 9:30 ገደማ መነሳቱን በመግለጽ፤ 4ኛው ፎቅ የሆቴሉ ምግብ ቤት መሆኑን ተናግረዋል።

በሕይወት የተረፉ ሰዎች በሆቴሉ የማንቂያ ደውሎች፣ የጭስ ጠቋሚዎች እና የእሳት አደጋ መከላከያዎች አለመኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ ጭስ ወደ 10 ኛ ፎቅ ድረስ መስፋፋቱን ተናግረዋል ሲል ኤፍ ፒ ዘግቧል።

Post image

እሳቱን ለማጥፋት 12 ሰዓታት መፍጀቱም የተነገረ ሲሆን፤ የሆቴሉን ባለቤት ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሊ ዬርሊካያ ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች ውስጥ 52ቱ መለየታቸውን በመግለጽ፤ የፎረንሲክ ቡድኖች የቀሩትን አስከሬኖች የመለየት ሥራ እየሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በቃጠሎው ወቅት ከተገኙት 238 እንግዶች መካከል 34ቱ በሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ 17ቱ ደግሞ ሕክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል ወጥተዋል ብለዋል።

Post image

ፕሬዚደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሀገሪቱ መንግሥታዊ ተቋማት የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በሀገሪቱ ብሄራዊ የሃዘን ቀን አውጀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ