ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በአክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ መደረጉን በፅኑ እንደሚያወግዝ በዛሬው ዕለት ወቅታዊ ነው ባለው ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ በአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ በማድረጋቸው በተወሰኑ ርዕሰ-መምህራን የተናጠል ውሳኔ ለፈተና እንዳይመዘገቡ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡
"ይህ ድርጊት ሕገ-ወጥ፣ የዕምነት ነፃነትን የሚጋፋ እንዲሁም ከሕግም ሆነ ከሀገራዊ እሴቶች ያፈነገጠ በመሆኑ በአፅንኦት እናወግዛለን" ሲል፤ በኢሕአፓ የትግራይ ክልል ፅ/ቤት በመግለጫው አስታውቋል።
"ተማሪዎቹ ለ12ኛ ክፍል ፈተና እንዳይቀመጡ መደረጉ እና ፍርድ ቤት ድርጊቱን እንዲያርሙ የሰጠውን ትዕዛዝ አለማክበራቸው ደግሞ፤ ሕገ-ወጥነት ስለሆነ በአፋጣኝ በሚመለከታቸው ክልላዊና የፌዴራል ባለስልጣናት አስገዳጅ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን" ሲልም ገልጿል።
በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ ከሰሞኑ "ይበቃል" በሚል እና እንዲሁም የሙስሊም ማህበረሰብ ከሂጃብ መልበስ ጋር በተያያዘ የሚያደርጓቸው ሰላማዊ ሰልፎችን በተመለከተ የጀመረው ትግል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰበው ፓርቲው፤ ዜጎችን መጠቀሚያ የማድረግ ድርጊት ሊቆም እንደሚገባም ተናግሯል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት መሆኑን በማንሳትም፤ "ሂጃብ እንዳይለብሱ በማድረግ በአክሱም ሴት ተማሪዎች የደረሰውን የመብት ጥሰት በማውገዝ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙትን ኃላፊዎች እና ርዕሳነ መምህራን ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው" ሲል አሳስቧል።
በአክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች፣ የጸጉር መሸፈኛ ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ፤ ተማሪዎቹ ለሳምንታት ትምህርት ቤት አለመሄዳቸው በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ እና ቅሬታን ፈጥሮ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡
ፍርድ ቤቱም ክልከላ የተደረገባቸው ተማሪዎቹ ሂጃብ ለብሰው የመማር መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም በክልከላው ምክንያት የምዝገባ ጊዜ አልፏቸው የነበሩት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ ያወሰነ ሲሆን፤ ተማሪዎችን ያገዱት ትምህርት ቤቶች ለጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎም በአክሱም ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ከሂጃብ ክልከላ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤት እና የትምህርት ቢሮ የተሰጠው ወሳኔና ትዕዛዝ እንዲተገበር የሚጠይቀውና የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በመቀሌ ከተማ በትናትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎም የትግራይ 20 የሚሆኑ የሙስሊም ማህበረሰብ ተወካዮች ከጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ "የሒጃብ ጉዳይ ፍጹም አጀንዳ መሆን የማይገባው ሆን ተብሎ አጀንዳ እንዲሆን የተደረገ ነው፤ በፍጥነት እልባት እንዲሰጠው እናደርጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ