ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ባንኮች የኢትዮጵያን ገበያ እንዲቀላቀሉ የሚፈቅድ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁ ይታወሳል፡፡

የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎም የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡

የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው ከፈለኝ ኃይሉ፤ "የውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ገበያን እንዲቀላቀሉ መፈቀዱ ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስ እና ጠቃሚ አሰራር ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

አዱሱ አሰራር ለባንክ ኢንዱስትሪው ሥር-ነቀል የሚባል ለውጥ መሆኑን ያብራሩት ባለሙያው፤ "የኢትዮጵያ ባንኮች በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዘርፉ ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ለኢትዮጵያ ቀጣይ ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙም ሲሆን፤ "ውሳኔው ወቅቱን የጠበቀና የኢንዱስትሪውን አሠራር አደረጃጀትና አጠቃላይ ይዘት የሚለውጥ ነው" ብለዋል።

አክለውም፤ "የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን እንደ አዲስ የሚያደራጁበትና ውሳኔውን ለመወጣት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳውቁበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የባንክ ባለሙያ ንጋቱ ወልዴ በበኩላቸው፤ "የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እያንዳንዱን የሀገር ውስጥ ባንክ ያነቃል" ብለዋል፡፡

"እያንዳንዱ የአገር ውስጥ ባንክ በውድድሩ ለመቀጠል በትኩረት እንዲሠራ ምክንያት ይሆናል" የሚሉት ባለሙያው፤ "ባንኮቹ ጠንካራ ካፒታል ከፈጠሩ እና ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ማስኬድ ከቻሉ ምንም ተፅዕኖ አይደርስባቸውም" ሲሉም ተናግረዋል።

ዘርፉ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ተቀባይነቱ የጎላ እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ ንጋቱ፤ የሥራ ዕድል ፈጠራውም የጎላ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ የውጪ ባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት እንዲሁም የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጥን በዓለም አቀፍ ልኬት መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡