ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ውስጥ በተሰራ ሥራ ከሕግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ፤ ከ2 ሺሕ በላይ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ወይም የባጃጅ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች የአዲስ አበባን መለያ ሰሌዳ እንዲያወጡ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ መለያ ሰሌዳ የሌለው የባጃጅ ተሽከርካሪ በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት መስጠት በሕግ የተከለከለ መሆኑን የጠቀሱት የቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪትና አደረጃጀት ዳይሬክተር አሸናፊ ስዩም፤ ከዚህ በፊት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ባጃጆች ሁሉም የክልል ሰሌዳ የነበራቸው መሆናቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል።

በመሆኑም የተሟላ ሰነድ በመያዝ የአዲስ አበባ ሰሌዳ ያወጡትን ከ2000 በላይ የሚሆኑ የባጃጅ አሽከርካሪዎችን ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ በማምጣት፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን ተደራጅተው ከመሀል ከተማው ወጣ ባሉ አካባቢዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በ2017 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በትራንስፖርት ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ በዋናነትም ከሕግ አግባብ ውጪ በከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የባጃጅ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን ወደ ሕጋዊ ስርዓት የማስገባት ሥራ በስፋት መሰራቱን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕግ ጥሰቶችንና የደንብ መተላለፎችን ለመከላከልና አገልግሎት አሰጣጡን ለመቆጣጠር እንዲያስችል በሚል ከነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ሰሌዳን ማውጣት ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህንን ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም የባጃጅ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ላይ በቢሮውና በሚመለከታቸው የእግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲመወስድ ማሳወቁ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ