ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ስደተኞችን በመጫን ከጅቡቲ የተነሳች መርከብ የመን አቅራቢያ ድባብ በተባለ ግዛት በደረሰባት የመስጠም አደጋ፤ 9 ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ የ20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕይወት ማለፉን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ።

መርከቧ 35 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከየመን ካፒቴን እና ረዳቱ ጋር አሳፍራ ከጅቡቲ ተነስታ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ከአራት ቀናት በፊት ቅዳሜ ጥር 10 ቀን 2017 ባጋጠማት ብርቱ ነፋስ በአል-ሀጃጃህ አካባቢ መስጠሟ ነው የተነገረው።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባወጣው መግለጫ፤ ከአደጋው 15 ኢትዮጵያውያን እና ሁለት የመናውያን የጀልባዋ ቀዛፊ እና ረዳቱ መትረፋቸውን ገልጿል።

በመን ውስጥ የድርጅቱ ተልዕኮ ኃላፊ የሆኑት አብዱሳተር ኢሶቭ፤ "ይህ አደጋ ለደህንነት እና ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚታለሉ በርካታ ስደተኞች የሚጋፈጡትን አሳዛኝ አደጋ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መደበኛ ያልሆነ የስደት መንስኤዎችን እንዲፈታ እና ለስደተኞች ጥበቃ እና ክብር ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

Post image

በርካታኢትዮጵያዊያ እና አፍሪካዊያን ስደተኞች በቀይ ባህር ላይ በማቋረጥ ወደተለያዩ የአረብ ሃገራት የሚሰደዱ ሲሆን፤ ይህም ተደጋጋሚ አደጋ እያደረሰ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ባለፈው ጥቅምት ወር ሦስት መቶ አስር ስደተኞችን ጭነው ከየመን የተነሱ ሁለት ጀልባዎች በጅቡቲ የባህር ጠረፍ አካባቢ ሰጥመው የ45 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ ከ60 ሺሕ በላይ ስደተኞችን በየመን መመዝገቡን የገለጸ ሲሆን፤ ከ2014 ጀምሮ በምስራቃዊ መስመር ላይ በመስጠም አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ 1 ሺሕ 416 ሰዎች ጨምሮ 3 ሺሕ 435 ሰዎች መሞታቸውን እና መሰወራቸውን አስታውቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ