ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከመስመር ውጪና አቆራርጠው በሚጭኑ እንዲሁም፤ ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"አሽከርካሪዎች ከትራንስፖርት ቢሮ ከተሰጣቸውና ከተመደቡበት መስመር ውጪ አዲስ መስመር በማውጣት፤ ባልተመደቡበትና የበለጠ ገንዘብ ሊሰበስቡበት የሚችሉትን መንገድ ብቻ በማሰብ ይሄዳሉ" ሲሉም ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
አንዳንድ ተራ አስከባሪዎች ከሹፌሩ ጋር በመነጋገር ተሽከርካሪውን ቀድመው ገንዘብ መቀበል በሚፈልጉት መስመር ብቻ እንዲሄድ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹም ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ አላስፈላጊ ለሆነ ረዥም ሰልፍ እየተዳረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም የአውቶቡስ ትራንስፖርት በሚጠቀሙበት ጊዜም፤ በታክሲ ሂሳብ ከማስከፈላቸው በተጨማሪ እነሱም ብዙውን ጊዜ ከመስመራቸው ውጪ እንደሚጭኑ ተናግረዋል።
"ችግሩን በአካባቢው ለሚገኙ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ብናሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" ሲሉም ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል፡፡
"ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እና በመሰል በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በሚፈጠር ተገቢ ያልሆነ አሰራር ለእንግልት ተዳርገናል" ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ "ይህም ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ የግድ መሄድ ስላለብን ብቻ ያለመስመራችን እየሄድን ከታሪፍ በላይ በመክፈል እጅግ ተቸግረናል" ሲሉ ተናግረዋል።
አሐዱም የነዋሪዎችን ቅሬታ ተቀብሎ የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮን አነጋግሯል።
የቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪትና አደረጃጀት ዳይሬክተር አሸናፊ ስዩም በምላሻቸው፤ "አሽከርካሪዎች በተቀመጠላቸው መስመርና ታሪፍ ብቻ መስራት አለባቸው" ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡም በተቀመጠው መስመር እና ታሪፍ መሰረት መገልገል እንዳለበት በማሳሰብ፤ "ይህንን ተግባራዊ በማያደርግ አሽከርካሪ ላይ ግን በተቀመጠው የአሰራር መመሪያ መሰረት ጥብቅ እርምጃ ነው ይወሰዳል" ሲሉ ገልዋል።
አክለውም ከዚህ ቀደም በ6 ወር ውስጥ ብቻ ከሕግ ውጪ በሚሰሩ ከ99 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ያስታወሱ ሲሆን፤ "ወደ ፊትም ችግሮችን ለማስተካከል ከቅጣት ባለፈ ሌሎች አስተማሪ የሚሆኑ መመሪያዎችን እያረምንና እያስተካከልን ነው የምንሄደው" ብለዋል።
"ሕግን በማያከብር ላይ በተለመደው ብቻ እየቀጣን የምንሄድ አይሆንም" ሲሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ አሽከርካሪው ሕግና ስርዓትን ጠብቆና ከትራንስፖርት ቢሮ የሚሰጠውን ወረቀት በግልፅ በሚታይ ቦታ ላይ ለጥፎ መስራት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ተጠቃሚውም ከሕግ ውጪ የሚንቀሳቀስ አሽከርካሪ ሲያጋጥመው በየአካባቢው ለሚገኝ የስምሪት ተቆጣጣሪ በማሳወቅ ተባባሪ መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
