ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሸገር ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የተቀመጠውን ደምብ በተላለፉ ከ54 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰዱን ለአሐዱ አስታውቋል።

በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ አደጋ ምክንያት በዜጎች ላይ ሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ለመቀነስ እና ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ እንግልት የሚዳርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያሲን አህመድ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም "ለትራፊክ አደጋ መከሰት የአሽከርካሪዎች ሥነምግባር ችግር እና የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ጉድለት ጉልህ ድርሻን ይይዛል" ብለዋል።

በእነዚህ የትራፊክ አደጋ መንሰዔዎች ላይ በተጠና እና በተጠናከረ መልኩ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅትና በትኩረት ቢሰራባቸውም እስካሁን ችግሩን መቅረፍ አለመቻሉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ጠጥቶ ከመጠን በላይ በፍጥነት ማሽከርከር ሌላኛው መንስኤ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ያሳስበኛል፣ ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም አካል የትራፊክ አደጋን ተቀዳሚ አጀንዳ እንዲያደርገውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።