ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያለ ጨረታ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እየተሰጡ፤ የግሉ ዘርፍ ከሥራ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ሲል የክልሉ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ገልጿል።

የአማራ ክልል ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ሙሉቀን ቢተው "በክልሉ የሚተገበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች 'ጨረታ አልወጣም' እንዳይባል ብቻ አምስት ያክል የመንግሥት ባለድርሻዎችን አሳትፈው፤ መልሰው የሚወስዱት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው" ሲሉ ለአሐዱ የገለጹ ሲሆን፤ ይህም ተግባር የግሉን ዘርፍ ይበልጥ እያዳከመው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ ከ6 ሺሕ በላይ ኮንትራክተሮች ችግር ውስጥ መሆናቸው በማንሳት፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱና በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላት ሥራቸውን መስራት እስካለመቻል የደረሱ ችግሮችን እያስተናገዱ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

"ችግሩ ከፍተኛ በመሆኑ በተለይም ያለው የሥራ ሁኔታ በቀዘቀዘበት እንዲሁም ፕሮጀክቶች ያለምንም ጨረታ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚሰጥበት ሁኔታ ውስጥ ኮንትራክተሮች ከፍተኛ ችግር ላይ እየወደቁ ነው" ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ በዚህም የተነሳ በርካቶች ቤታቸውን፣ ማሽኖቻቸውን፣ መኪኖቻቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ ከ6 ሺሕ በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ቢኖሩም በማህበሩ ሥር የታቀፉት 755 አካባቢ ብቻ መሆናቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ወርሃዊ መዋጮ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ አባላት ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡

የለመዱንት ሥራ ትቶ ወደ ሌሎች ዘርፎች መሰማራት ፈታኝ መሆኑን ያነሱት አቶ ሙሉቀን፤ "ይህን ዘርፍ ትተው ሌላ ሥራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ ላይሆኑ የሚችሉ ባለሙያዎችም አሉ፤ ስለዚህም ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አሐዱም "የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ እንዲህ አይነት ችግሮችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በምን መልኩ ነው የሚቆጣረው? እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ ሳያውቅ የአካባቢው እና የክልል ኃላፊዎች እንዲህ አይነቱን ተግባር እንዳይፈፅሙ ምን ድርሻ አላቸው?" ሲል የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ የትምጌታ አስራትን ጠይቋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት ምላሽ፤ "አስቸኳይ እና በልዩነት የመንግሥት የልማት ድርጅቶት እንዲገቡባቸው የሚያስፈልጉ ቦታዎች ካልሆኑ በስተቀር፤ በሌሎቹ ፕሮጀክቶች ላይ ሁሉም በጨረታ እንዲሳተፉ ይደረጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ፤ የአማራ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር፤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግሩን መግለጹን፣ ነገር ግን እስካሁን የመፍትሄ አለማግኘቱን አስታውቋል።