ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ የግጭቱ መንስኤ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት ይገባል ሲል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን፤ በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶች ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጠ መሆኑን አንስተው፤ "መንግሥት ሰፊ የሆነ የሰላም ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።


አክለውም በየጊዜው ለሚፈጠሩ ግጭቶች እና አለመግባባቶችን መፍታት ብቻ ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ ገልጸው፤ "የችግሩ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም ሀገራዊ ውይይቶች ስለስላም የሚሰብኩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ፤ በሁሉም ማህበረሰብ እኩል ተቀባይነት ያላቸውን ጉዳዮች በመለየት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ እንደሚቻል አንስተዋል።

"በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለው ጥረት የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት እንጂ መንስኤዎቹ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ባለመሆኑ ለውጥ እየታየ አይደለም" ብለዋል።

በዚህም መሠረት የችግሩ መንስኤ ላይ በሰፊው መሰራት እንደሚገባ አንስተው ያለውን እውቀት፣ ጊዜ፣ ሀብት እና ጉልበት ፈሰስ በማድረግ ሰላም በሚያመጡ ውይይቶች ላይ መሰራ እንደሚገባ አቶ አህመድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን ግጭት ለመፍታ ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ "ሰላም እንዴት ማምጣት ይቻላል" የሚሉትን ጉዳዮች መመልከት እንደሚገባ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ከችግሩ ይልቅ መንስኤው ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።