ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሉበትን ሁኔታ መገምገሙን አስታውቋል።

በጦርነት ምክንያት በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን ከየፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነትን በሗላ የኮረ ከተማ፣ አላማጣ፣ ዋጃ ጡሙጋ ቀበሌ ሌሎችም ቦታዎች ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው መገለጹ ይታወሳል።

ተፈናቃዩቹ ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኃላ መሠረታዊ አገልግሎት እና የሰብዓዊ ድጋፍ አለማግኘታቸውን እና በጸጥታ ሥጋት ምክንያት ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ አሁንም ድረስ በትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ መኖራቸውን፤ በኮሚሽኑ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

ዳይሬክተሯ ተፈናቃዩቹ ማህበራዊ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን አንስተው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በፈረቃ ትምህርት መስጠት የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን እና የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት መቸገራቸውን እና ቅሬታ የሚያቀርቡበት ቦታ አለመኖሩን አንስተዋል።

በቀጣይ የሚከናወኑ ተፈናቃዮችን ወደቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ተግባር እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የማድረግ ሂደት የሰብዓዊ መብቶች መስፈርቶችን መሠረት ያደረገ እና ያሟላ መሆኑ በቅድሚያ ሊረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ