ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሜሪካ በዋሽንግቶን ዲሲ በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3:00 ላይ፤ 64 ሰዎችን ይዞ ሲበር የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን በሮናልድ ሬገን አየር ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ ከጦር ሄሊኮብተር ጋር ተጋጭቶ መከስከሱ ተሰምቷል።

የፒ.ኤስ.ኤ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥሩ 5342 የሆነውና 60 መንገደኞችን እና 4 የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው ቦምባርዲየር CRJ-700 አውሮፕላን ሬገን ዋሽንግተን ብሔራዊ ኤርፖርት ለማረፍ በተቃረበበት ሰዓት 3 የአሜሪካ ጦር አባላትን ከያዘ ወታደራዊ ሂሊኮፕተር ጋር በመጋጨቱ፤ 'ፖቶማክ' በተሰኘ ወንዝ ላይ መከስከሱ ነው የተገለጸው።

የሕይወት አድን ጀልባዎች እና ጠላቂዎች በወንዙ ውስጥ የገቡ ሰዎችን በፍለጋ ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ የሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ለጊዜው የአውሮፕላን በረራ ማስተናገድ ማቆሙም ተነግሯል።

Post image

አደጋ የደረሰበት የመንገደኞች አውሮፕላኑ መነሻውን ከዊቺታ ካንሳስ አድርጎ መዳረሻውን ወደ ዋሽንግተን እንደነበር ተገልጿል።

የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ እስካሁን ስለ ሞቱ ሰዎች የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለና የነፍስ አድን ሥራ ላይ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

አደጋውን ተከትሎ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ አደጋውን "አሰቃቂ አደጋ" ሲሉ ገልጸውታል።

አክለውም "በመጀመሪያ ምላሽ ሰጪዎቻችን እየሰሩት ላለው አስደናቂ ሥራ እናመሰግናለን፣ ሁኔታውን እየተከታተልን ሲሆን ተጨማሪ ዝርዝሮችን እንሰጣለን" ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዜዳንት ጄዲ ቫንስ በበኩላቸው፤ ከአሰቃቂው አደጋ ሰዎች እንዲተርፉ ሁሉም በጸሎት እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።

Post image

የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የአደጋውን ምክንያት እና ዝርዝር ጉዳዮች አስመልክቶ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

በ2009 በቡፋሎ ኒው ዮርክ የአየር ክልል ላይ የንግድ አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ፤ ዛሬ ፓቶማክ ወንዝ ላይ የወደቀው የመጀመሪያው የንግድ አውሮፕላን መሆኑን የሲቢኤስ ኒውስ ዘገባ አመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ