ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፊታችን የካቲት አንድ እና ሁለት 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት፤ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር ከፍተኛ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።

ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እይታ፣ የፖሊሲ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ባሉ ጉዳዮች እንዲሁም እየተካሄዱ ባሉ ማሻሻያዎች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም የገንዘብ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡

በተጨማሪም በጉብኝቱ ኢትዮጵያ ከግሉ ሴክተር ተወካዮች ጋር፤ በሀገሪቱ ስላለው የንግድ ሁኔታ እና የኢኮኖሚ ዕድሎች ሃሳብ እንደሚለዋወጡ ተመላክቷል።

ጉብኝቱ አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የጋራ እና ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በፖሊሲዎች ላይ ውይይት ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገኝ እንደሚያግዝም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በፈረንጆቹ 2019 ከተሾሙ በኋላ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ይሆናል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ