ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለ አገልግሎቱ ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚደረግ የድሮን እና ሌሎች በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ ለአሐዱ በላከው መግለጫ፤ በአዋጅ ቁጥር 1276/2014 በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።
ተቋሙ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ስጋቶች ለመከላከል የሚያስችል በቂ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።
ሥራው ውጤታማ እንዲሆንም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ጠንካራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚፈልግ ጠቁሟል፡፡
በተለይ ከመጪው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ቅንጅቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ፤ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማኝናውም አይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል መግለጫው አመልክቷል፡፡
በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም አስፈላጊ ከሆነ ጠያቂው አካል የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን አይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ አስቀድሞ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን መጠየቅ እና ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባውም አስታውቋል፡፡
ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዘፈቀደ የሚነሱ እና የሚበሩ ድሮኖች ካሉ ተቋሙ አዲስ አበባንና ዙሪያዋን በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ ያጠረ በመሆኑ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ ድሮኖቹን ከአየር ላይ በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የድሮን አብራሪዎቹን በቁጥጥር ሥር በማዋል ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ከሥራ ጋር በተያያዘ ድሮኖችን መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም አካል በ+251 983 00 02 98 እና +251 983 00 04 01 ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችልም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማንኛውንም አይነት ድሮን ያለፈቃድ ማስነሳትም ሆነ ማብረር እንደማይቻል ተገለጸ
አዲስ አበባና ዙሪያዋ በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ መታጠሩ ተገልጿል