ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የሰጡት መግለጫ አንድን አካል ብቻ የሚደግፍ ነው ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ እና ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ወታደራዊ አመራሮችና ፓርቲዎች ከፖለቲካዊ ጉዳይ እጃቸውን ማንሳት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ሃይሉ ከበደ "አሁን ላይ በትግራይ ያለው ሠራዊት በአንድ አካል ብቻ እንደተፈለገ የሚዘወር አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ "ወታደር የወታደሩን ሥራ ብቻ እንዲሰራ መተው አለበት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአመራሩ አካሄድ ተገቢ ባይሆን በተለይም ግን ከሥር ያሉት አባላት ቅሬታቸውንና 'ይህ ሂደት ትክክል አይደለም' የሚል ሀሳባቸውን መስጠታቸውን የገለጹም ሲሆን፤ "አሁን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል" ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ የከፍተኛ ጦር አመራሮቹ አካሄድን የሚቃወም እንዲሁም ደግሞ የሚደግፍ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልሎች ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን በተመለከተ ሀሳባቸውን የሰጡት የባይቶና አባይ ፓርቲ ሊቀመንበር ክብሮም በርሄ በበኩላቸው፤ "ባለፉት ጊዜያት የተደረገው መግለጫ ከጦር አመራሮች የሚጠበቅ ሥራ አይደለም" ብለዋል፡፡
"በትግራይ አሁንም ቢሆን የተረጋጋ ሁኔታ የለም" የሚሉት አመራሩ፤ ከፌደራል መንግሥት እና ከኤርትራ ጋር አሁንም ያልተጠናቀቁ ችግሮች መኖራቸውን በመግለጽ "ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ነገር ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በትግራይ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉት ፖለቲካዊ ቀውሶች እንዲፈቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም ቁርጠኛ መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ