ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የግልግል ዳኝነት ተቋማትን ለማቋቋምና ተግባራዊ ለማድረግ የአመዘጋገብ፣ ፍቃድ አሰጣጥና ቁጥጥርን በተመለከተ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊላክ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተዘጋጀው በዚህ ረቂቅ ደንብ ላይ ከፍርድ ቤት፣ ጠበቆች፣ ከዩኒቨርስቲ ተወካዮች እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙባቸው የተለያዩ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ገልጿል።
ረቂቅ ደንቡን ለማዘጋጀት ባለፉት ዓመታት ሰፋ ያለ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱንና በ2016 ዓ.ም በተደረገ የመጀመሪያ ውይይት ከባለሙያዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓቶችን በማካተት፣ ተጨማሪ ጥናት በማድረግና በማሻሻል ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን በሚኒስቴሩ የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል ሄኖክ ተስፋዬ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህን ረቂቅ ደንብ ለማውጣት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት፤ ከጠበቆች፣ ዳኞች እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችና ጥናቶችን በማድረግ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
አክለውም የግልግል ዳኝነትን በሚመለከት የቀረበው ረቂቅ ደንብ ከጸደቀ በኋላ፤ ጥያቄ ላቀረቡ ማህበራት እና ተቋማት የፍቃድ እና የምዝገባ ሂደቶች በቀጣይ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
የግልግል ዳኝነት ማዕከላት የሚመሩበት ወጥ የሆነ ሕግና ደንብ ማዘጋጀት አስፈላጊነቱን ያብራሩት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በተለይም ንግድ ነክ በሆኑ ጉዳዩች ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ግልፅ የሆነ አሰራር ለማዘጋጀት ታሳቢ ተደርጓ የተቀረጸ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተቋማዊ የግልግል ዳኝነት ማዕከላት የተደራጀ ያለመግባባት መፍቻ አገልግሎትን ለመስጠት፣ በዘርፉ ምርምር በማድረግና የአቅም ግንባታ ሥራ ለመስራት፣ ውሳኔዎች ሙያዊ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፍትህ ስርዓት እድገትን ማገዝና ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሏቸውም ተገልጿል።
የረቂቅ ደንቡ ዋና አላማም ዓለም አቀፍ ጀረጃውን የጠበቀ ማዕከል እንዲኖር ማስቻል፣ ግልፅ መስፈርቶችን መደንገግና የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ግልፅ የቁጥጥር ስርዓት መፍጠር መሆኑ በረቂቅ ደንቡ ተመላክቷል።
በተለይም በንግድና በኢንቨስትመንት ጉዳዮች ዙሪያ ለሚነሱ አለመግባባቶች ለመፍታት የግልግል ዳኝነት ማቋቋም አስፈላጊ ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የግልግል ዳኝነትና የዕርቅ አሠራርን ለመተግበር "ኢትዮ ሌግጀሪ ሆምስ ኃ/የተ/የግ/ማሕበር" የተሰኘ የዳኞች ስብስብ፤ የመተዳደሪያ ደንብና የዳኞችን ዲሲፕሊን ሥርዓት አዘጋጅቶ ፍቃድ ለማግኘት ለፍትህ ሚኒስቴር ጥያቄ በማቅረብ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ