ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሸገር ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ነዋሪዎች መሠረተ-ልማት በበቂ ሁኔታ ባለመሟላቱ ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ ለአሐዱ አስታውቀዋል።
"የውሀ እና የመብራት አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ አልተሟሉልንም" የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ "ተመጣጣኝ ባልሆነ ዋጋ በችርቻሮ የሚሸጠው ውሃም ለመጠጥ የማይሆን እና ለቆዳ በሽታም የሚዳርግ ነው" ብለዋል።
የመብራት አቅርቦትን በተመለከተም 35 አባወራ ለሚገኝበት አንድ ሕንጻ በአንድ ቆጣሪ ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነ እና ይህም የኃይል ማነስ እንዳስከተለ ነግረውናል። "ያለው ኃይል ለአምፖል ብቻ የሚያገለግል በመሆኑ ምግብ ለማብሰል ከሰል እና እንጨት ለመጠቀም ተገደናል" ብለዋል።
ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በልማት ተነስተው ኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸውና ከቀደመ አካባቢያቸው ሲነሱ በቂ የመሠረተ ልማት እንደሚሟላላቸው ተገልጾ፤ ቃል የተገባላቸው ሳይተገበር ላለፉት 2 ዓመታት ችግር ላይ እንደሚገኙም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
መፍትሄ ፍለጋ ያመለከቱባቸው የመንግሥት ቢሮዎችም መፍትሔ እንዳልሰጧቸው፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ኮሚቴም ከየአንዳንዱ ነዋሪ ገንዘብ ቢሰበስብም ገንዘቡ የገባበት እንደማይታወቅ አብራርተዋል።
አሐዱም ለቅሬታ አቅራቢዎቹ አቤቱታ ምላሽ ለማግኘት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ኮሚቴ ያነጋገረ ሲሆን፤ "ላለፉት 2 ዓመታት ነዋሪዎቹ ችግር ላይ መሆናቸው ከታወቀ ለምን መፍትሔ አልተሰጣቸውም? የተዋጣው ገንዘብስ ምን ላይ ዋለ?" ሲል ጠይቋል።
የ160 ብሎክ የኮሚቴ ሰብሳቢ ሴና ቤካ በምላሻቸው፤ ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ችግሮች እንዳለ አምነው፤ "በተለይም የውሀ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ የለም" ብለዋል።
አክለውም፤ የመብራት ችግርን ከዓመት በፊት መፈታት መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ "ሙሉ በመሉ የውሀና የሀይል አቅርቦትን ለመፍታት ከመንግሥት አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ነዋሪዎቹ ምንም ዓይነት የልማት መዋጮ እንዳላዋጡ አብራርተዋል። "ኮሚቴዎቹ ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ነዋሪዎች መካከል የተመረጡ በመሆናው የውሃ እና የመብራት ችግሩ ገፈት ቀማሾች ናቸው" ብለዋል።
ሰብሳቢው አያይዘውም ከመንግሥት ጋር የተጀመሩ ሥራዎች በቅርቡ ስለሚጠናቀቁ ነዋሪዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም አሐዱ የሸገር ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ቢሮን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን፤ የቢሮው የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ በላይ በቀለ ችግሮች ሲፈጠሩ በጋራ መኖሪያ ቤት ኮሚቴዎች በኩል የሚፈቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ "ይህም ጉዳይ ከኮሚቴው አቅም በላይ እስካልሆነ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ ጣልቃ አይገባም" የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡