ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በቀጣይ ሳምንት ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡለትን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክብ አስታውቋል፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ታምራት ሀይሉ ምክር ቤቱ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን አጀንዳዎቻቸውን እንዲያስገቡ ጥሪ ማቅረቡን የገለጹ ሲሆን፤ አሁንም የማስገቢያው ጊዜ እስኪጠናቀቅ ማስረከብ እንደሚቻል ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኘ የተናገሩት አቶ ታምራት፤ ‘አልሰማንም' የሚል ወቀሳ እንዳይመጣ በተለያየ መንገድ የማሳወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሚቀርቡለትን አጀንዳዎች ከመገናኛ ብዙሃኑ በመቀበል፤ በቀጣይ ሳምንት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተጠመረውን እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል፡፡
"‘ጥሪ አልደረሰኝም' ከሚሉት መካከል ምክር ቤቱ አባል ያለሆኑ መገናኛ ብዙሃን ይገኙበታል" የሚሉት አቶ ታምራት፤ ነገር ግን አሁን ‘ማንኛውም አጀንዳ አለኝ‘ የሚል አካል ማስረከብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
"ለመሆኑ ምክር ቤቱ ምን ያህል አጀንዳዎችን ተረክቧል የተነሱ አጀንዳዎችስ ምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው?" ሲል አሐዱ ለምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
አቶ ታምራትም በምላሻቸውም እስካሁን 79 የሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች እንደተሰበሰቡ ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ አጀንዳዎች ውስጥም 19 የሚሆኑት የተመረጡ ሲሆን፤ በቀጣይ ወደ 5 እና 6 በማሳጠር አጀንዳውን የማስረከብ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ይህንን ይበል እንጂ አሐዱ ያነጋራቸው የመገናኛ ብዙሃኖች አጀንዳ አለማስረከባቸውን እና በምክር ቤቱም አጀንዳ እንዲያስገቡ አለመጠየቃቸውን አሐዱ አስታውቀዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በቀጣይ ሳምንት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን እንደሚያስረክብ አስታወቀ
