ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች የተፈጸሙና በምርመራ የተረጋገጡ ከባድ የመብት ጥሰት ስነዶችን የሽግግር ፍትህ የፍርድ ሂደት በሚጀምርበት ወቅት እንደማስረጃነት እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንደገለጹት፤ ከፍተኛ የሆኑ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ በክትትልና በምርመራ የተገኙ ሰነዶች ለማስረጃነት ጭምር የሚቀመጡ ናቸው።

Post image

በተጨማሪም ከፍርድ ሂደቱ ባሻገር ለሚፈጸሙ የእርቅ ሂደቶች እና ችግሮች በቀደምው ወቅት እንዴት እንደሚፈቱ አቅጣጫዎችን ለማመላክት ማስረጃዎች ተሰንደው እንደሚቀመጡ ተናግረዋል።

"ኢሰመኮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና አቤቱታዎችን በአካል፣ በስልክ እና በሶስተኛ ወገን የሚቀበልበት የአሰራር መንገድ ያለው ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

አክለውም በአማራና አንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ምክንያት በሚፈለገው ልክ ሥራዎችን ተንቀሳቅሶ ለመስራት አዳጋች እንዳደረገበትና የክትትልና ምርመራ ሥራዎችን መስራት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እንዲሁም ወቅታዊ ሪፖርቶችን የሚያወጣ ሲሆን፤ "እነዚህ መረጃዎችም 'ወደፊት ይደረጋል' ለተባለው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጠቃሚ ግብዓቶች ይሆናሉ" ተብሏል፡፡

ተግባራዊ የሚደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት "የወንጀል ምርመራ በማካሄድ እና ክስ በመመስረት አጥፊዎች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት የሚዘረጋ ይሆናል" ሲል ፖሊሲው ያትታል። ምርመራ እና ክስ የሚከናወነው "በጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ ያተኮረ" እንደሚሆን በፖሊሲው ላይ ሰፍሯል።

የፖሊሲውን አብዛኛው ክፍል የሚሸፍነው እና ሁለተኛው ክፍል የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባር፣ የምህረት፤ ማካካሻ፤ ተቋማዊ ማሻሻያ፤ የሚሉ ቁልፍ ነጥቦችን ያቀፈ ሲሆን፤ ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ ወሰን የተመለከቱ አንኳር የሽግግር ፍትህ ስልቶችን ያቀፈም መሆኑ ይታወቃል።