ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ማኅበራት በኢትዮጵያ፣ በጅቡቲና አካባቢው የንግድና የሎጅስቲክስ ኮሪደር ቢዝነስ ለማበልፀግ የሚያስችል ኮንፈንስ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በትናንትናው ዕለት ተጀምሮ 40 ተወካዮች እና 100 የዘርፉ ተዋናዮች እየተሳተፉበት በሚገኘው የ2 ቀናት መድረክ ላይ፤ "የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ቀጠናዊ ጥያቄዎችን ለማሟላት የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደርን ማሳደግ ያስፈልጋል" ተብሏል።
በዚህም ሁለቱ ሀገራት ለበርካታ ጊዜያት የንግድና የሎጅቲክስ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሹ እና ግንባር ቀደሙ መሆኑም ተመላክቷል።
የኢትዮ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት ኤልሳቤጥ ጌታሁን በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ "የኮንፍረንሱ ዓላማ የኢትዮጵያና ጅቡቲን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር እንዲሁም ለሁለቱም ሀገራት ዘላቂ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የንግድ ሽርክናዎችን ማመቻቸት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
"የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ከራሳቸው ባለፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጠቃሚ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"ጅቡቲ ጠንካራ የሆነ የወደብ አቅም አላት" ያሉ ሲሆን፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳላት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እያቋቋመች መሆኑ ውጤታማ የዘመነ የሎጅስቲክ አሠራር መፍጠር ከተቻለ ለኢትዮጵያ ብሎም ለማዕከላዊ አፍሪካ ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል። አክለውም "የሀገራቱ ግንኙነትም ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ዘርፍ በዘንድሮው የዓለም ባንክ መመዘኛ ውስጥ ያልተካተተ ቢሆንም፤ ዘርፉ መሻሻሎችን እያሳየ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የመሠረተ ልማት ውስንነትን መፍታት፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማዳበር፣ የወደብ መጨናነቅን መቀነስ እንዲሁም የቀይ ባህር ቀውስን ማረጋጋት ላይ በጋራ በትኩረት ሊሰሩባቸው ይገባል" ሲሉም አስስበዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የትራንስፓርትና ሎጂስቲከስ ሚኒስቴርን ጨምሮ የጅቡቲ መንግሥት ውሳኔ ሰጪዎችና አመራሮችን፣ የንግድ መሪዎች፣ አምራቶች፣ አስመጪና ላኪዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች በኮንፍረንሱ ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚህም ኮንፍረንሱ በሀገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት፣ የዕውቀት ልውውጥ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሎጅስቲክ ዘርፍ ማኅበራት በሎጅስቲክ ሰንሰለት ውስጥ የማማከር፣ የገንዘብና መድኅን ሽፋን አገልግሎት የሚሠጡ እንዲሁም የሎጀሰስቲክስ አገልግሎትን በተመለከተ ሕግ የሚያወጡ፣ የሚቆጣጠሩና ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን በአንድ ላይ አሰባስቦ የተቋቋመ ማኅበር ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ