ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በደማቁ የሚከበረው የከተራና ጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ ፖሊስ ከሚሰራው መደበኛ የፀጥታ ሥራ ባሻገር፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
በበዓሉ ዕለትም ከሀይማኖታዊ ስርዓቱ ባሻገር የብሔር ብሔረሰቦች አለባበስ እና ሌሎች ባህላዊ ትዕይንቶች እንደሚኖሩ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለአሐዱ ገልጸዋል።
አክለውም "ከሀይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱ ውጪ የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በዘፈንና ግጥም መግለፅ፣ ቲሸርት ላይ በማሳተምና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም በአሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ መግባት ፈፅሞ የተከለከሉ ናቸው።" ያሉ ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ለሁሉም የፀጥታ አካላት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጠው አስታውቀዋል።
በዘንድሮው በዓል 66 የታቦታት ማረፊያ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ 274 የሚሆኑ ታቦታት ደግሞ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ማረፊያ ቦታዎች ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለው ገልጸዋል።
"በዚህም መሰረት ታቦታቱ በሚያርፉባቸው ቦታዎች ላይ በቂ የፀጥታ ሀይል በግልፅና በስውር ጥበቃ ያደርጋል" ብለዋል።
በተጨማሪም ወዲያው ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች በየቦታው ስለሚቋቋሙ በቅርበት በመሆን ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከልና ከተፈፀመም ወዲያውኑ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚደረግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።
አያይዘውም በተለይም በጥናት በተለዩ ቦታዎች ላይ ፍተሻና አሰሳ ስለሚደረግ ህብረተሰቡ በተቻለ አቅም በዓሉ ሰላማዊ እንዲሆን ፖሊስ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች በመደገፍና በመተባበር ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጥምቀት በዓል ከሀይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱ ውጪ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች በፍፁም የተከለከሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ
በዘንድሮው በዓል በመዲናዋ 66 የታቦታት ማረፊያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል