ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጥምቀት በዓልን በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበሉ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ተናግረዋል።

በጎንደር የሚከበረውን ልዩ የጥምቀት በዓል አስመልክቶ ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት መግለጫ የሰጡት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው "ጎንደር ለወራት የዘለቀ የጥምቀት በዓል ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች" ብለዋል።

Post image

ጎንደር በጥር ወር እጅግ የምትደምቅበት እና በርካታ ሁነቶች የሚከናወኑት ወቅት መሆኑን ገልጸው፤ የባህልና የኪነጥበብ ፌስቲቫል እንዲሁም የጎንደር ባህል የሆነው ትያትር ዛሬ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በርካታ እንግዶች ጥምቀትን ለመታደም እየመጡ ሲሆን፤ ከነገ ጥር 10 ቀን 2017ዓ.ም ጀምሮ ሐይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

Post image

"የጎንደር ጥምቀት ከ400 ዓመታት ታሪክ ካለው ጥምቀት ባህር የሚከበር በመሆኑ የጎንደር ጥምቀትን ልዩ ያደርገዋል" ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ "እንግዶች በዓሉን ከማክበር ባለፈ በቆይታቸው በጎንደር የሚገኙ ከ7 በላይ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በመኖራቸው ለቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ አይረሴ ያደርገዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ጎንደር ካሏት ታሪካዊ ቅርሶች የፋሲል አብያተ መንግሥት እና ሌሎች ቅርሶችን በተጨማሪ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት መሆኑን መናገራቸውን ከከተማዋ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Post image

ለሚመጡ እንግዶች ተጨማሪ በረራ በማስፈቀድ በርካታ እንግዶች እየገቡ ሲሆን፤ የከተማው ሕዝብ እንግዶችን ለመቀበል የቤተሰብ ትስስር መፈጠሩንም ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል ኢኮኖሚያዊ ፋንዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የኢንቨስትመንት ዘርፉ በጥምቀት በዓል በልዩ ትኩረት የሚሰራ ሲሆን ጥር 13 ቀን 2017ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፎርም መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ