ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጅ የሲቪል ሠራተኞች ከጦርነት በኃላ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመግባት ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ መሰናበታቸው እንደተነገራቸው የኢትዮጵያ የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የትግራይ ቅርጫፍ ለአሐዱ አስታውቋል።
የቅርጫፍ ፅ/ቤቱ ኃላፊ ጸሐዬ እምባዬ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ የአፋር ክልል የሠራተኞች መመሪያውን ተከትሎ ማመልከቻ በመለጠፍ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸውን እንዲመለሱ ቢጠይቅም፤ ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ባለመመለሳቸው ከሚሰሩባቸው ተቋማት ተሰናብተዋል።
ይሁን እንጂ ሠራተኞቹ ከአፋር ክልል በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ትግራይ የተመለሱ መሆናቸውን በማንሳት፤ "ይህንን ከግምት ማስገባት ተገቢ ነበር" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል እና በትግራይ ክልል መካከል በጎ የሚባል ግንኙነት በመፈጠሩ ይህንን ችግር እና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለክልሉ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ጉዳዩንም ለዋናው ዕምባ ጠባቂ ተቋም እና አፋር ክልል ቅርንጫፍ ዕምባ ጠባቂ ፅ/ቤት በማንሳት ምላሹን እየጠበቁ መሆኑንም ኃላፊው ለአሐዱ ገልጸዋል።
የትግራይ እምባ ጠባቂ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጅ የሲቪል ሠራተኞች ብቻም ሳይሆን በክልሉ በአሁን ሰዓት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የአየር ሀይል አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ከጦርነቱ በኃላ በሥራ ላይ የነበሩ ሠራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በክልሉ ከ900 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የሚገልጹት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ እስካሁን ወደ ቀያቸው ባለመመለሳቸው ምክንያት ከፍተኛ ቀውስ በክልሉ ላይ መፍጠሩን ለአሐዱ አስረድተዋል።
"ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም በክብር ከተሸኙ በኃላ ጡረታ እንዲዘጋባቸው መደረጉ አግባብነት የለውም በሚል ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር ግንኙነት እየተደረገ ነው" ብለዋል።
ይሁን እንጂ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላትን በተመለከተ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምላሽ ለማግኘት አለመቻሉንም እምባ ጠባቂ ተቋሙ ለአሐዱ ገልጿል።
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ይሰሩ የነበሩ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸውንና የበርካታ ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው መዘገባችን ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ