ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የምርት አቅርቦት እጥረት ሳይፈጠር ምርት በመደበቅ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ በአንዳንድ ነጋዴዎች ምክንያት የምርት እጥረት እንዲያጋጥም ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ የህብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተለይም በበዓላት ወቅት ለሚስተዋሉ የምርት እጥረት እና የዋጋ መወደድ፤ ምርትን በመደበቅ በገበያ ላይ እጥረት እንዲያፈጠር እና ዋጋ እንዲጨምር በሚያደርጉ በአንዳንድ ነጋዴዎች ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የምርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ እና ዋጋ በመጨመር ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረገው የአሰራር ችግር ለመፍታት፤ አምራች እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የንግድ ሰንሰለቱን የማሳጠር ሥራ እየተሰራም እንደሚገኝ የኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጥላሁን ጌታቸው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የገና በዓል መቃረቡን ተከትሎ፤ በሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ላይ የሚሸጡ ምርቶች ላይ ዋጋ መወሰን የማይችሉበት አሰራር መኖሩን የገለጹም ሲሆን፤ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ በምርቶች ላይ እጥረት እንዳያጋጥም ከአምራቾች ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከምርት አቅርቦትና ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በየክፍለ ከተማው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በ11 ከተሞች ላይ 164 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የሚገኙ ሲሆን፤ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶች ከአምራቹ ወደ ሸማቹ በቀጥታ እንዲደርስ እና የንግድ ሰንሰለቱ እንዲያጥር እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ በሸማቹ ላይ አላስፈላጊ ወጪ እንዳይጫን የመከላከል ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የምርቶችን ዋጋ ማውጣት እና የመቆጣጥር ኃላፊነት እንደሌለው የተነገረ ሲሆን፤ በከተማዋ በሚገኙ 137 የገና ባዛሮች ላይ ምርቶች ለገበያ መቅባቸውን እንዲሁም ከ8 መቶ በላይ የሚሆኑ የመቸርቸሪያ ሱቆች አገልግሎት እየተሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡