ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የምርጫ ስርዓት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን በሚመለከት የተሻሻለው አዋጅ ክፍተቶች እንዳሉበት፤ በኢትዮጵያ ብሐራዊ ምርጫ ቦርድ ጋባዥነት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተሳተፉ ፓርቲች ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አስመልክቶ በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መደረጉ ይታወሳል።
'ከዚህ ቀደም የነበረዉ አዋጅ ማሻሻያ ያስፈልገዋል' በሚል በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተደረገ ግብዣ በቀጥታ የሚመለከታቸው ፓርቲዎች ተገኝተው ሀሳብ ሰጥተውበታል።
በውይይቱ የነጻነት እና የእኩልነት ፓርቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የተገኙ ሲሆን፤ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ ላይ ክፍተቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
ማሻሻያውን በሚመለከት በውይይቱ ላይ ከተገኙት ፖርቲዎች አንዱ የሆነው የኢዜማ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ዋሲሁን ተስፋዬ ከአሐዱ መድረክ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ያሉት አዋጆች ክፍተቶቻቸው ታይቶ የሚሻሻሉበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም እንዳልነበረ አንስተዋል፡፡
ነገር ግን የተሻሻለው አዋጅ ቀደም ብሎ ረቂቁ ለፓርቲዎች ደርሶ መታየት አለመቻሉ ትልቅ ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል።
"በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምርጫ ጣቢያን ከመወሰን አንጻር ያለው ገደብ እንዲሁም ሕዝበ ወሳኔ እንደ አንድ የምርጫ አይነት አለመካተቱ፤ በአዋጁ ላይ ከተስተዋሉ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው" ሲሉም የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው በአዋጁ መሻሻል ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀት እና አቅም ግንባታ ኃላፊ ሙባረክ ረሺድ በበኩላቸው፤ "የአብላጫ ድምጽ ስርዓትን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል በቅድሚያ ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ይኖርበታል" ብለዋል።
አክለውም "የምርጫ ስርዓቱን የማስተካከል እና ምቹ ስነ ምህዳር ለመፍጠር እንዲሁም ፍትሀዊ የምርጫ ስርዓትን ለመፍጠር ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሱ ክፍተቶችን በአጽንኦት ሊመለከት ይገባል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
"የተሻሻለው የምርጫ ስርዓት እና የተሻለ አሰራር ሲኖር የዜጎችን አመኔታ ይጨምራል" የሚሉት አቶ ሙባረክ፤ ቅድመ ሁኔታዎች በተሻለ መልኩ እንዲተገበሩ የአዋጁ መሻሻል ተገቢ እና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የፓርቲዎቹ ተወካዮች አክለውም፤ አዋጁ ከዚህ ቀደም በስፋት ሲነሱ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እንዲችል ከመሻሻሉ በፊት በማሻሻያ ሀሳቦቹ ላይ በተነሱት ነጥቦች ላይ ፓርቲዎች መወያየት እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፤ አሁንም የሚስካከሉ ነገሮችን ለማረም ከምርጫ ቦርድ ጋር እንደሚነጋገሩ አሳውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ