ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሊባኖስ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 359 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ እና ለአደጋ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የመመለስ ሥራ መቀጠሉን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ በሳምንቱ 156 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ከሊባኖስ ወደ ሀገር የተመለሱት 156 ዜጎች 143 ሴቶች 13 ጨቅላ ሕጻናት ሲሆኑ፤ ከተመላሾች መካከል 18 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል ተብሏል።
በተያያዘ ዜና በሳምንቱ 185 ወንዶች፣ 15 ሴቶች 3 ጨቅላ ሕጻናት በድምሩ 203 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ከተመላሾች መካከል 4 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል።
ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ሥራም እየተሰራ እንደሚገኝ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ከሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎችን የመመለስ ሥራ እስካሁን 90 ሺሕ 101 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉም ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ