ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ለቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አከባቢዎች ቢኖሩም፤ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዘርፉ እክል እየሆኑ መምጣታቸውን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።
"ክልሉ ባሉት ሀብቶች ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ቢሆንም፤ የጸጥታ ችግሮች ከመሰረተ ልማት አለመመቻቸት ጋር ተደምሮ በቂ ጎብኚ ማግኘት እንዳይችሉ እያደረገ ነው" ሲሉ የቢሮው ኃላፊ ወይኒቱ መልኩ ተናግረዋል።
አክለውም ችግሮች የሚከሰትባቸው አካባቢዎችና ወቅቶች ተለይተው ከጸጥታ አካላት ጋር በርካታ ቅንጅታዊ ሥራዎች ቢሰሩም ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቁመዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማቱን ለማስፋት በተለይም ከበጀት ጋር ተያይዞ የሚታዩ እንከኖች ራስን ችሎ ለመስራት ክፍተት እንደፈጠረ አብራርተዋል።
በዚህም ኃላፊዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማሻሻል ከዘርፉ የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ለማግኘት ሁሉም አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኃላፊዋ አያይዘውም በክልሉ ውስጥ ያለውን የቱሪስት መስህብ ለማስተዋወቅ እና የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ