ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰባት ጋዛ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 73 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።

እስራኤል እና ሃማስ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት በመጪው እሁድ ጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለ ሲሆን፤ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት መቀጠሉ ተነግሯል።

ሁለቱ ወገኖች የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ከእስራኤል በኩል የምክር ቤቱን ይሁንታ ማግኘት አለበት ተብሏል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ረቡዕ፣ ጥር 7/2017 ዓ.ም. ይፋ መሆኑን ተከትሎ፤ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 73 ፍልስጤማውያን በአንድ ምሽት መገደላቸውን በሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።

Post image

ከተገደሉት መካከል በጋዛ ከተማ ሼክ ራድዋን ሰፈር በአንድ መኖሪያ ሕንጻ ነዋሪ የነበሩ 12 ሰዎች እንደሚገኙበት የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ በደቡባዊ እስራኤል "የወደቀ ሚሳኤል" ማግኘቱን መጀመሪያ ላይ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ግን ስህተት ነው ብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም. የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት በፓርላማ ያጸድቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ ጽህፈት ቤታቸው "ሃማስ የስምምነቱን አንዳንድ ክፍሎች "እንደሻረ" በመግለጽ "የመጨረሻ ደቂቃ ቀውስ" እንዲፈጠር አድርጓል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ሐማስ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እስካልተቀበለ ድረስ ካቢኔው እንደማይሰበሰብም ጽህፈት ቤታቸው አክሏል።

የሃማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሃማስ በአደራዳሪዎቹ ይፋ ለተደረገው ስምምነት ቁርጠኛ መሆኑን እና የልዑካን ቡድኑ መሪ ኻሊል አል ሃያ የስምምነቱን ውሎች ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውን ለኳታር እና ግብፅ በይፋ አሳውቀዋል ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ