ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጅማ ከተማ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰባት ሕጻናት በወላጆቻቸው ተጥለው መገኘታቸውን፤ የከተማው ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ አስታውቋል።

በከተማዋ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት አላስፈላጊ ቦታዎች ላይ ጥሎ መሄድ ከየትኛውም ጊዜያቶች በላይ እየተባባሰ መምጣቱን የቢሮ ኃላፊ ኢክራም አብዲ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ችግሩን ለመቅረፍ በግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ቢሰራም መፍትሔ ማምጣት አለመቻሉን አንስተዋል።

ለችግሩ መስፋፋት የወላጆች ኢኮኖሚያዊ ገቢ አነስተኛ መሆንን እንዲሁም አላስፈላጊ እርግዝና መከሰት መንስኤ መሆኑን አብራርተዋል።

የተገኙትን ሕጻናት በማቋያ መሠረታዊ ነገሮች ተሟልቶላቸው የቆዩ ሲሆን፤ በሕጋዊ መንገድ ለሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ቤተሰቦች እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሕጻናቱን በጉዲፈቻ ተቀብለው ለማሳደግ የሚያመለክቱ ወላጆች ሕጻናቱን ከመረከባቸው በፊት የኢኮኖሚ አቅማቸው፣ ማኅበራዊ ተቀባይነታቸው እና ሌሎች ሁኔታዎች በባለሙያዎች እንደሚገመገሙም ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ኢክራም አብዲ አክለውም "በወላጅ ወይም በአሳዳጊዎች በተለያየ ጊዜ እና ቦታ ተጥለው የተገኙ ሕጻናትን መንግሥት ከተረከበ በኋላ ወደ ማቆያ ማዕከላት ያስገባቸዋል፤ አሳዳጊ ወላጆች በማፈላለግም ቅድመ ሁኔታውን ለሚያሟሉ ወላጆች ሕጻናቱን ያስረክባል" ብለዋል፡፡

በማዕከል ውስጥ ሕጻናትን በመንከባከብ፣ በመጠበቅ እና በማስተማር ደረጃ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑንም ነግረውናል።

አያይዘውም ከክልሉ መንግሥት ጋር የችግሩን መንስኤ በማጣራት እልባት ለመስጠት እየተሠራ ነው ያሉ ሲሆን፤ በከተማዋ የችግሩን መንሰራፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከታቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ነገሮች እግዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሕጻናትን ወልደው የሚተው ወላጆች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም የቢሮ ኃላፊ ኢክራም አብዲ አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ