ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ውስጥ አስገዳጅ ደረጃ ከወጣባቸውና የጥራት ቁጥጥር ከተደረገባቸው ገቢ ምርቶች ውስጥ የኢትዮጵያን የጥራት ደረጃ ያላሟሉ ከ9 መቶ 32 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

ማንኛውም ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ሀገሪቷ ባስቀመጠችው ደረጃ መሰረት ድንበር ላይ ፍተሻ እንደሚደረግ ለአሐዱ የተናገሩት በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊቁ በነበሩ ናቸው፡፡

መሪ ሥራ አስፈፃሚው በርካታ ምርቶችም የኢትዮጵያ ደረጃ ባለማሟላታቸው ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የማድረግ ሥራ መሰራቱንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያን የጥራት ደረጃ ሳያሟሉ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችም፤ በየፍተሻ ጣቢያው የሚገኙ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አንፃር በሚፈጥሩት ክፍትት እንደሆነ ተናግረዋል።

በቅርቡ ከሁለት ሳምንት በፊትም አስገዳጅ የኢትዮጵያን ደረጃ ያላሟላ የተሸከርካሪ ባትሪ ወደ ሀገር እንዲገባ ያደረጉ ባለሙያዎች ከሥራ መሰናበታቸውንና ጉዳያቸው በሕግ እየተጣራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

መሰል ሕገ-ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ሚደረገው የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡

በጠቅላላው ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን 700 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ገቢ እቃዎች ላይ የጥራት ቁጥጥር ሥራ ስለመደረጉም ኃላፊው አመላክተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ