ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ለመምህርነት ሙያ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያደርገውን የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ከሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አዳምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) "ረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ትምህርትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ ያስችላል" ብለዋል።

Post image

በተጨማሪም "የመንግሥትን የትምህርት ስርዓት ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ያደርጋል" ነው ያሉት።

ረቂቅ አዋጁ ለመምህርነት ሙያ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ሴት መምህራንን ወደ አመራርነት እንዲመጡ የሚያበረታታና አካቶ ትምህርትን አስገዳጅ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

Post image

በረቂቅ አዋጁ ላይ ቋሚ ኮሚቴውና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውንና በዚህም 77 አንቀፆች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጁ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በ2 ተቃውሞ በ10 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አዋጅ ቁጥር 1368/2017 ሆኖ ጸድቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ