ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሶማሊያ ጦር ባለፈው ማክሰኞ በሂራን ክልል ምስራቃዊ ክፍል በወሰደው እርምጃ 16 የአል-ሸባብ ብድን አባላትን መግደሉን የሀገሪቱ የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ጦር ኃይሉ በሀገሪቱ ከሚገኙ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን የአል ሸባብ ታጣቂዎች ቡድን ለማጥፋት በሂራና ክልል የጀመረውን መጠነ ሰፊ ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠሉ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም የሀገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ቢራ ያባል፣ ቡር አቦቶ፣ ኤጋ ጋልማአይ፣ ጂድቺላን እና ካዶው ጉሬይ ጨምሮ በርካታ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን በተሳካ ሁኔታ መያዛቸው ተነግሯል።

በዚህ ወታደራዊ ዘመቻም 16 የሚደርሱ የሽብር ቡድኑን ታጣቂዎች መግደሉን ጦሩ አስታውቋል፡፡

ሠራዊቱ እስካሁን እያደረገ ያለው ዘመቻ ሶማሊያን ከአክራሪ ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማውጣት እና የሶማሊያ ዜጎችን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ተገልጿል።

ሀገሪቱ ለዓመታት ከሽብር ቡድኖች ጋር እየታገለች ብትገኝም፤ የዜጓቿን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻለችም ነው የተባለው፡፡

አል-ሸባብ ከአሮፓዊያኑ 2007 ጀምሮ ከሶማሊያ መንግሥትንና በሀገሪቱ ከሰፈረውን የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች ጋር እየተዋጋ ይገኛል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ