መጋቢት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በባህላዊ መንገድ ከሚዘጋጀው አንጻር 45 በመቶ ብክነትን የሚከላከለው የእንሰት አዘገጃጀትን የሚያዘምን ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ መግባቱን አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
ወደ ሥራ የገባውና እንሰትን በዘመናዊ መንገድ የሚያዘጋጅው ቴክኖሎጂ፤ የሴቶችን የሥራ ጫና የሚያቃልል እና በጉልበት ሥራው ምክንያት የሚደርስባቸውን አካላዊ ጉዳት የሚያስቀር መሆኑንም ነው ዩንቨርስቲው የገለጸው፡፡
በባህላዊው መንገድ ከሚዘጋጀው አንጻር 45 በመቶ ብክነትን የሚከላከለው አዲሱ ዘመናዊ ማሽን፤ 15 ሴቶች በከባድ የጉልበት ሥራ በአንድ ቀን የሚያዘጋጁትን የእንሰት ምርት በ2 ሰዓት እንደሚሰጥ ተነግሮለታል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ-ዳይቨርሲቲ ሪስርችና ኮንሰርቬሽን ሴንተር ዳይሬክተር ዶክተር ሽቴ ጋተው ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀው ማሽን እንሰቱን መፋቅ፣ መጭመቅ፣ የተፋቀውን እንሰት ማጣራት፣ ወደ ዱቄት መቀየርና ማብላላት የሚያስችል ነው፡፡
አክለውም፤ አዲሱ ቴክኖሎጂ እንሰቱ ከተፋቀ በኋላ ለምግብ አገልግሎት ለመዋል ይፈጅበት የነበረውን ከ3 እስከ 1 ዓመት የተራዘመ ጊዜ ወደ 7 ቀን ማሳጠር ችሏል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከል የተዘጋጀውን የእንሰት ማምረቻ ማሽን ማኅበረሰቡ በስፋት እንዲገለገልበት ሴቶችን በማኅበር በማደራጀት እያስረከቡ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ቆጮ ለመስራት የሚያገለግለውን እንሰት በዱቄት መልክ ተዘጋጅቶ ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝና ለውጭ ገበያ የማቅረብም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሽቴ ተናግረዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንሰትን በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ከ20 ሚልዮን በላይ ዜጎች ለምግብነት ይጠቀሙታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ