መጋቢት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 300 መቶ ሴት ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ላይሙዓለ ንዋያቸውን ፈሰስ እያደረጉ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ ገልጿል።
በሚኒስቴር መ/ቤቱ በግብርና ዘርፍ የሙዓለ ንዋይ (ኢንቨስትመንት) ገበያና ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደረጄ አበበ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ሴቶች በአሁኑ ወቅት በአራቱም በግብርናው ዘርፎች ተሰማርተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህም "ሴቶች በእርሻ፣ በከብት እርባታ፣ በሆርቲካልቸር እና በኮንትራት ግብርና ዘርፍ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው" ብለዋል።
እንደ ሀገር አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙ ግጭቶች ሴት ባለሃብቶች ላይ የሚፈጠረው ጫና የጎላ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፤ "ሴት ባለሃብቶች ሙዓለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሴት ባለሃብቶች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ለሥራው የሚሰጡት ትኩረት የላቀ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ "በዚህ ምክንያት ከሞላ ጎደል ለኪሳራ የመጋለጥ አቅማቸው የከፋ አይደለም" ብለዋል።
አክለውም መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን በመግለጽ፤ በተለይም ሴት ባለሃብቶች የሚያሳዩትን ተነሳሽነት አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከ6 ሺሕ በላይ ባለሃብቾች በግብርናው ዘርፍ መሰማራታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህ ባለሃብቶች በአማራ፣ በኦሮሚያና፣ በአፋር ክልሎች በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
300 ሴት ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ላይ መሰማራታቸው ተገለጸ
