መጋቢት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት በመሆን በይፋ የተሾሙት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሹመታቸውን ተከትሎ "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድ"ን ፈርመወል፡፡
ሰነዱም፡-
1. የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት፣ በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ፤
2. በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፤
3. በክልኩ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት፤
4. መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲሣለጡ ማድረግ፤
5. ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤
6. ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፤ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት፣ የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ደሞክራሲያዊ ዐውድ እንዲፈጠር መሥራት፤
7. የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤
8. የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትሥሥር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚሉ ሃሳቦችን ይዟል፡፡
ጄነራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት በመሆን ሥራቸውን ሲጀምሩ ከላይ የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶችን በትጋት እና በታማኝነት ለመወጣት ቃል ገብተው ፈርመዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሹመታቸውን ተከትሎ "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድ" ላይ ፊርማቸውን አኖሩ
