መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የማስተር ካርድ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊዮት የተመራ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ልዑክ፤ በኢትዮጵያ አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስጀመርና የትብብር ዕድሎችን ለመፈተሽ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት አካሂዷል።

የትብብር ማዕቀፉ የቴሌብርን እና የማስተር ካርድን ፕላትፎርሞችን በመጠቀም፤ የዲጂታል ፋይናንስ መፍትሄዎችን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋት እና ዘላቂ እድገትን ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

Post image

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ትልቅ የደንበኞች ቁጥር እና ግዙፍ መሠረተ ልማት ያለው በመሆኑ፤ ይህም አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ እንደፈጠረለት ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ከማስተርካርድ ጋር በአጋርነት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊዮት በበኩላቸው፤ የኢትዮ ቴሌኮም ፈጣን የደንበኞች ቁጥር ዕድገት እና ግዙፍ የመሰረተ ልማት አቅም ለአጋርነት ተመራጭ እንደሚያደርገው በመግለጽ፤ ማስተርካርድ ይህ ትብብር መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት መሆኑን እና ለተግባራዊነቱ ያላቸውን የላቀ ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Post image

ይህ ስትራቴጂያዊ ትብብር የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ፣ ዘላቂ ዕድገትንና የሀብት ፈጠራን በማበረታታት አካታች እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳር እንዲሁም ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል ስለመሆኑም ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ