መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችን የሙዚቃ ሥራዎች ለንግድ አላማ የሚጠቀሙ ድርጅቶችና ተቋማት፤ የ'ሮያሊቲ'ን ሕግ አለመረዳታቸው ክፍተት እንደፈጠረበት የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ማናቸውንም ወጥ እና ትርጉም የኪነ ጥበብ ሥራዎችን መዝግቦ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የተናገሩት የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኤልያስ መሀመድ ናቸው።

በቅጂ መብት ጥበቃ ላይ ደጋግመው ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከልም ሙዚቃን ገቢ ለሚያስገኝ ዓላማ የተጠቀሙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የ'ሮያሊቲ' ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸው መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም የሮያሊቲ ክፍያ በሌሎች ሀገራትም እየተሰራበት የሚገኝ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዳይደረግ በዘርፉ ተዋንያን ዘንድ ሮያሊቲን የመረዳት ችግር እንዳለ አንስተዋል።

Post image

ማናቸውም ሙዚቃን ለንግድ አላማ ያዋለ ድርጅት ወይም ግለሰብ ለሥራው ባለቤቶች ክፍያ መፈጸም እንደሚገባው የሚደነግግ ሕግ ቢኖርም፤ "ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ከሥራዎቻቸው ተጠቃሚ ለመሆን ማኅበር ያቋቋሙ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማገዝ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ኃላፊው እንደገለጹት ሮያሊቲ ክፍያን ለማስጀመር ለንግድ ተቋማት፣ ለመገናኛ ብዙኃን፣ ለጂጄዎች እና ለሌሎችም የማሳወቅ ሥራዎች በመሰራት ሲሆኑ፤ "ከምክክር ሂደቱ በኋላ ወደ ተግባራዊነቱ እንገባለን" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ