መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ምዝገባ ስርዓት ዳግም መጀመሩ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በክልሉ የተቋረጠውን አገልግሎት ዳግም ለማስጀመርም ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የመቀለ ክላስተር ማስታወቁ ይታወሳል።

አሐዱም ይህንን መነሻ በማድረግ "በክልሉ የተቋረጠው አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲመለስ ምን እየተደረገ ነው?" ሲል የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎትን ጠይቋል።

በአገልግሎቱ የአባላት አስተዳደርና ሀብት አሰባሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጉደታ አበበ ሰጡት ምላሽ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የጤና መድህን አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲመለስ በተጠና ጥናት የሕዝቡ ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ፤ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከክልሉ ጋር በመሆን ሰፊ የንቅናቄ ሥራ እየተሰራ ነው።

የሰው ኃይል ቅጥርን በተመለከተና ሕግና ደንብ ማውጣትን ጨምሮ አጠቃላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ በማድረግ የዝግጅት ሥራው መጠናቀቁንም ጨምረው ገልጸዋል።

አክለውም በዚህ ዓመት አዲስ አበባንና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ሁሉም ክልሎች ላይ በሙሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጽ፤ በትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ ስራውን ለማስቀጠል የአባላት ምዝገባ ስርዓት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩልም የጤና መድህን ምዝገባና እድሳቱ በየዓመቱ ከመስከረም እስከ የካቲት መጨረሻ የሚከናወን እንደነበረ ጠቅሰው፤ በዘንድሮው ዓመት በተለያየ ምክንያት ላላጠናቀቁ ክልሎች እስከ መጋቢት 30 ድረስ እንዲራዘም መደረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ምዝገባና እድሳቱን ካጠናቀቁት ከአዲስ አበባ፣ ሲዳማ፣ ሀረር እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ክልሎች እስከ መጋቢት 30 ድረስ የምዝገባና የእድሳት ሥራውን ማጠናቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ