መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ከአጎራባች እና ከክልል ከተሞች 6 ሺሕ የከተማ ታክሲዎች በድጋፍ ሰጪነት ወደ ከተማዋ መግባቱን የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪት አደረጃጀት ዳይሬክተር አሸናፊ ስዩም ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት ከሚሰጡ ታክሲዎች መካከል በቁጥር የሚበዙት ከክልል ከተሞች በድጋፍ ሰጪነት የገቡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

ኃላፊው አክለውም "የእስከ አሁኑ አሰራር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተና አስገዳጅነት የሌለው ነበር" ያሉ ሲሆን፤ ውሉ አስገዳጅ ባለመሆኑ አገልግሎት ሰጪዎቹ ባሻቸው ጊዜ ውላቸውን አቋርጠው ይወጡ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ይህ መሆኑ ደግሞ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

"ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የአዲስ አበባ ኮድ አንድ ተሽከርካሪዎች ረዥም ጊዜ አገልግሎት በመስጠታቸው የተገልጋዩን ፍላጎት ማርካት አልቻሉም" ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት ከአጎራባች እና ከክልል ከተሞች 6 ሺሕ የከተማ ታክሲዎች በድጋፍ ሰጪነት ወደ ከተማዋ ገብተው አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የከተማዋን ነዋሪ የትራንስፖርት ፍላጎት ለመሙላት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም የቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪት አደረጃጀት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ