መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ- አዳማ፣ በድሬዳዋ- ደወሌ፣ በሞጆ -ባቱ እና ሌሎች የክፍያ መንገዶች የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በድምሩ 850 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ማለትም (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻና ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ) ከ140 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱን፤ በኢንተርፕራይዙ የሕዝብ ግንኙነትና የማርኬቲንግ ክፍል ማናጀር ተመስገን ጎዳና ለአሐዱ ገልጸዋል።

በዚህም በ6 ወራቱ ከክፍያ መንገድ አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 850 ሚሊዮ ብር በመሰብሰብ ለፌዴራል መንግሥት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

ገቢው ከሌሎች ጊዜያት አንፃር ሲስተያይ የተሻለ እንደሆነም ጨምረው አብራርተዋል።

እንዲሁም፤ ከአዲሳባ -አዳማ ፈጣን መንገድ ጥገናን በተመለከተ ከ500 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎ ከ78 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና መደረጉን አስታውሰዋል።

የመንገዶቹን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮች በማዘጋጀት፣ በማስተማር እና በመንገድ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ የትራፊክ አደጋን መቀነስ ስለመቻሉም ኃላፊው ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ