መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የታክሲ አሽከርካሪዎች መመሪያን ባልተከተለ እና ያለ በቂ ምክንያት በትራፊኮች ፖሊሶች እየተቀጡ መሆኑን ለአሐዱ ባቀረቡት ቅሬታ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በትራፊኮች በሚጣልባቸው አላግባባብ እንደተማረሩ የገለጹት የታክሲ አሽከርካሪዎቹ፤ አዲሱ የቅጣት ማሻሻያ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ሥራቸውን በአግባቡ ለመስራት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በቂ ያልሆኑ ምክንያቶችን በማቅረብ በየጊዜው እስከ 1 ሺሕ 500 ብር ድረስ ለቅጣት እንደሚከፍሉና በዚህም ምክንያት ሰርተው የቀን ገቢ ለማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም ሁሉም የታክሲ ሹፌር ከሕግ በላይ እንዳልሆነና ጥፋት ከተገኘም በመመሪያው መሠረት በማስረጃ ሊሆን እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ ባልሆነበት መንገድ ያለ በቂ ማስረጃ 'ደንብ ተላልፈሀል' በሚል ብቻ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል እንዳሆነ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ገቢያቸው በመቀነሱ ቤተሰብ ለማስተዳደር እንደተቸገሩ እና በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አሐዱም ይህንን ችግር በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና የሕዝብ ግንዛቤ ድቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነን ጠይቋል፡፡
ኃላፊው በምላሻቸው የእርምጃ አወሳሰዱ በአዋጅ በወጣው መመሪያ መሠረት የወጡ ደንቦችን ተግባራዊ ስለመደረጉ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህም የወጡ ደንቦችን የሚጥሱ አሽከርካሪዎች ላይ የሚወሰድ እርምጃ እንጂ ሆን ተብሎ የሚደረግ የቅጣት እርምጃ እንደሌለ አንስተው፤ በተለይ ብቃት ሳይኖራቸው የማሽከርከር ፍላጎት ስላላቸው ብቻ እና ንብረታቸውን ለሌላ አካል አሳልፈው በመስጠት በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ የቅጣት መመሪያም እንደየ ጥፋትና ደንብ መተላለፍ የሚወሰን መሆኑን አንስተው፤ በተለይ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሚያሽከረክሩ እና ለሌላ አሳልፎ መስጠት እስከ 8 ሺሕ ብር የሚያስቀጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በመንገድና ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ተግባዊ ለማድረግ የሚወጡ መመሪያዎች አለመከበራቸው በሥራ ላይ ተግዳሮት እየፈጠረ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው፤ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚወጡ መመሪያዎች እና ደንቦችን የማክበር ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።
የትራፊክ የትራፊክ አደጋ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ የሚወጡ መመሪያዎችም ተግባራዊ እንዲሆኑ እና የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላል በጋራ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
መመሪያውን ባልተከተለ እና ያለ በቂ ምክንያት እየተቀጡ መሆናቸውን የታክሲ አሽከርካሪዎች ገለጹ
