የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥነት ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች ቶሎ ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ በግልጽ ማሳሰቢያ መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ዛሬ ከሰዓት በሆላ ከነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ መወያየታቸውን በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

በዚህም ውይይት ላይ በነዳጅ ኩባንያዎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት አደረጃጀቶች በኩል ያሉ ውስንነቶች መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

"መንግሥት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ብዙ ቢሊዮን መዋእለ ንዋይ እየደጎመ ነዳጅን አቅርቧል" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "በዚህ መልኩ የገባን ነዳጅ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያን እንዳሻቸው ሊያደርጉ ከቶውንም አይገባም" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ በሕገ-ወጥነት ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች ቶሎ ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ በግልፅ ማሳሰቢያ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

አክለውም "በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተን ነዳጅን በሕገወጥ መንገድ ጨለማን ተገን በማደረግና በችርቻሮ የሚሰራጭበትን መንገድ ለማስቆም የጀመርነውን እርምጃዎች አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም "ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትን በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረጉ ጥረቶች እንደማንታገስ በግልጽ አሳውቀናል" ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ጨክነን ተገቢውን እርምጃ እየወሰድን እንሄዳለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ