የካቲት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ብቻ በጠቅላላ ከ2 ሺሕ በላይ ሰዎችን የያዙ 83 የአቤቱታ መዝገቦች መቅረባቸውን የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም ትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ፀሀዬ እምባዬ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ከቀረቡት 83 የአቤቱታ መዝገቦች ውስጥ በቀጥታ የእንባ ጠባቂ ተቋሙን የሚመለከቱት 29 መዝገቦች ብቻ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ የግል ጉዳይ፣ ፍርድ ቤት የሚመለከታቸውና በምክር ቤት የተወሰኑ እንዲሁም በቂ መረጃ ባለመያዛቸው ምላሽ ያልተሰጠባቸው አቤቱታዎች መሆናቸውን አሳውቀዋል።

በተጨማሪም ተቋሙን ከሚመለከቱ 29 መዝገቦች ውስጥ 7 በመቶ የሚሆኑት ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።

ከቀረቡት የአቤቱታ መዝገቦች ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃውን የሚይዙት የሥራ ማጣት፣ ከሥራ መባረር እንዲሁም ቅጥርን የሚመለከቱ አቤቱታዎች ሲሆኑ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ "አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም" የሚሉ አቤቱታዎች መሆናቸውን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሌሎች አቤቱታዎች፤ የመሬት ይዞታና የጡረታ መብትን የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይም በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችና ተገልጋዮች፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በርካታ ቅሬታ እንዳላቸው መስተዋሉን አንስተዋል፡፡

ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ 24 የሚሆኑት ውሳኔ ማግኘታቸውን የገለጹም ሲሆን፤ በሂደት ላይ ያሉ አቤቱታዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዚህ ዓመት ሦስት ክሶች መመስረታቸውን የገለጹት የጽ/ቤቱ ኃላፊ፤ ሁለቱ ክሶች ሲቆሙ አንደኛው ክስ ግን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መላኩን ተናግረዋል።

ክሶች የቆሙበት ምክንያት ሲያስረዱም "እንባ ጠባቂ ተቋም ከሚመራባቸው ደንቦች መካከል ደንብ አራት ሥራ እንዳይሰራ ያስቆመው ጉዳይ በመኖሩ" ነው ብለዋል።

የጽ/ቤት ኃላፊው የትኞቹ ክሶች እንደተቋረጡና የትኛው ክስ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደተላከ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ