መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ ሲሸጡ በነበሩ 22 ሰዎች በእሰራት እንዲቀጡ እና 24 ማደያዎች ላይ እርምጃ ማድረጉን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው የኢንስፔክሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቆጲሳ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር እያለ 'የለም' በሚሉ እና ከተቀመጠው የዋጋ ተመን በላይ በሕገ-ወጥ ሲሸጡ በነበሩ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከየካቲት ወር ጀምሮ ሕገ-ወጦችን ለመቆጣጠር አዲስ ግብረ ሃይል ማቋቋሙን አስታውሰው፤ በዚህም ከፍተኛ ለውጥ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ በተቋቋመው ግብረ-ሃይል እና ቅንጅታዊ አሰራር መሠረት 24 ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።
ከ24ቱ ማደያዎች መካከል 4ቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲታሸጉ መደረጉን አንስተው፤ ሌሎችን አስተዳደራዊና የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በመቱ ከተማ አንድ ማደያ፣ በሻሸመኔ ከተማ 2 ማደያዎች እንዲሁም በሐረርጌ 1 ማደያ እንዲዘጉ ተደርገዋል ብለዋል።
እንድሁም የማደያ ባለቤቶችን ጨምሮ 22 ግለሰቦች በእስራት እንድቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃ የጹሁፈ ማስጠንቀቂያ እና ንብረቶቻቸውን በመውረስ የተወሰደባቸው እንዳሉም አያይዘው ገልጸዋል።
አክለውም በክልሉ በ7 ወራት ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ360 ሺሕ ሊትር በላይ ቤንዚል እና ከ86 ሺሕ 400 ሊትር በላይ ናፍጣ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በአጠቃላይ ከ446 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር እንድውል መደረጉንም አያይዘው ገልጸዋል።
በክልሉ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር ከባለ ድርሻ ተቋት ጋር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም የክልሉ ንግድ ቢሮ የኢንስፔክሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቆጲሳ ለአሐዱ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኦሮሚያ ክልል በ1 ወር ውስጥ ብቻ በሕገ-ወጥ ነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ 22 ሰዎችና 24 ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
አራት ማደያዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲታሸጉ ተደርጓል
