መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፈር ጥራትን፣ የጤና እና ጤና ነክ ጉዳዮችን እንዲሁም የድምጽ መጠንን የሚለኩ ደረጃዎች በተያዘው በጀት ዓመት ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንዲፀድቁ ሊደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢንስቲትዩቱ በሰባት ዘርፎች ተዋቅሮ ደረጃ የሚመድብ መሆኑን የገለጹት በኢንስቲትዩቱ በደረጃ ዝግጅት ዘርፍ የአካባቢ ጤናና ደህንነት ደረጃ ዝግጅት ዴስክ ኃላፊ ወርቁ አደፍርስ፤ ከዚህም እንደ አካባቢ ጤናና ደህንነት ዘርፍ፣ የአፈር ጥራት፣ የጤናና ጤና ነክ እንዲሁም ከድምጽ ጋር ተያይዞ የደረጃ ዝግጅት ሥራዎች መኖራቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ማሻሻያው ያስፈለገው ጊዜያቸው አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ደረጃዎች በአሰራሩ መሠረት፤ በድጋሚ መታየት ስላለባቸው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ጊዜ የሚያመጣቸው ፍላጎቶችን ከመመለስ አኳያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ይዘቱ ሲቀየር እንዲሁም የቴክኖሎጂን ጨምሮ የባለሙያ ለውጥ በሚኖርበት ሰዓት የማህበረሰቡና የተቋማቱ አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
የደረጃ ማሻሻያ ከሚደረግበት ውስጥ የአፈር ጥራት መለኪያ ለግንባታ፣ ለእርሻና መሰል አገልግሎቶች የሚውል እንደየ አይነቱ የደረጃ አወጣጥ ሲኖረው፤ የጤናና ጤና ነክ ጉዳዩችን በተመለከተም የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማትን ጨምሮ ከጤና ጋር ግንኙነት ባላቸው ተቋማት በሙሉ የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከድምጸት ጋር በተያያዘ የሰውን ልጅ ጤና እንዳይነካ ሆነው የሚወጡ በርካታ አይነት ደረጃዎች እንዳሉት የጠቀሱት ኃላፊው፤ ለአብነትም ፋብሪካ ውስጥ ከማሽኖች የሚሰማዉን የድምጽ መጠን ገደብን ጨምሮ የበርካታ ድምጾች ደረጃ የሚወስን መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መሠረት ማሻሻያው ላይ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሳተፉ ተደርጎ መዘጋጀቱን በማንሳት፤ በቀጣይ ብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ቀርበው እንዲፀድቁ ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አፈር፣ የጤና እና የድምጽ ደረጃዎች በድጋሚ ሊሻሻሉ መሆኑ ተገለጸ
