መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሆቴልና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልን እያሳየ ቢሆንም፤ በሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ላይ የተማረ ብቁ የሰው ሃይል እጥረት መኖሩ ይነሳል።

ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩት የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብሩክ ታደሰ፤ በዘርፉ ላይ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።

"በዚህ ጉዳይ ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ" ያሉት ኃላፊው፤ "በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ እያለ ሥራ ማግኘት ያልቻለ ሲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ተቁማት ደግሞ የባለሙያ እጥረት መኖሩን ያነሳሉ" ብለዋል።

ለዚህም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በየዓመቱ በሚያደርገው ጥናት ግን በዘርፉ ብቁ የባለሙያዎች እጥረት መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

አሑዱም "ማህበሩ ብቁ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት ስልጠናዎችን ይሰጣል ወይ?" ሲል ጠይቋል።

ማህበሩ መደበኛ የሆነ ስልጠና እንደማይሰጥ ገልጸው፤ "በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞችን ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የማሳደጊያና አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ብቻ ይሰጣል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ስልጠናም የሆቴል ኢንዱስትሪ ከብዙ ዘርፍ ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ፤ የሚወጡ አዳዲስ ደረጃዎችን መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሆቴል ኢንዱስትሪ ማስልጠኛ ተቋማትም ቢሆን በሚፈለገው ልክ አለመኖራቸው፤ ብቁ የሰው ሃይል ላለመኖሩ ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ብሩክ ታደሰ ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት ብሎም ለማዘመን ከሚመለክታቸው ተቋማትና ሙያተኞች ባለድርሻ ጋር እየተሰራ ቢሆንም፤ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የሰው ሃይል ችግር ግን ለመቅረፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እምብዛም መሆናቸውን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ