የካቲት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይ ዳግም ምዘና ተደርጎ የኮከብ ደረጃ ሊሰጥ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለ ንብረቶች ማህበር አስታውቋል፡፡
በዚህም በመዲናዋ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች የደረጃ መስፈርትን ለመቀበል ምን ማሟላት አለባቸው? የሚለውን በተመለከ፤ ዳግም ምዘና እንደሚካሄድ የማህበሩ ፕሬዝደንት አስቴር ሰለሞን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በሆቴሎች ላይ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሂደቱ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቷ፤ በርካታ ሆቴሎች ደረጃ ሳይወጣላቸው አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በመሆኑም በከተማዋ ላይ በሚገኙ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ላይ ዳግመኛ የደረጃ ምዘና በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ "የደረጃ ምዘናው ሂደቱ በአንድ ሆቴል ላይ አንድ ቀን ሊወስድ ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባለ ኮከብ ሆቴሎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው ምክንያት ደረጃ የማያገኙበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም አንስተዋል፡፡
የምዘና ሂደቱ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚደረግ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ሆቴል ባለ ንብረቶች ማህበር በተወካይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አዲስ በሚደረገው የደረጃ ምደባ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ያስቀመጣቸውን አስገዳጅ መስፈርቶችን በሚመለከት ምዘና እንደሚደረግ የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ "ይህም አቅማቸውን ለመለየት እና ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል" ብለዋል።
የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደረጃ ምደባ ደንብ፤ ሆቴሎች በየሦስት ዓመቱ በዳግም የደረጃ ምደባ ሂደት ማለፍ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ሆቴሎች ላይ ዳግም ምዘና ተደርጎ ደረጃ ሊሰጥ መሆኑ ተገለጸ
