የካቲት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በየካቲት 12 ሆስፒታል ድንገተኛ ሕክምና የሚፈልጉ ታካሚዎች ባለው የምርመራ መሳሪያ እጥረት ምክንያት በበቂ ሁኔታ አገልግሎቱን እያገኙ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡

በቀን ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ዜጎች ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል እንደሚያመሩ፤ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ድንገተኛ እና ጽኑ ህሙሟን ህክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሞላልኝ ውባንተ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በድንገተኛ የትራፊክ አደጋ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዲሁም ተላላፊ ባልሆኑ ሕመመሞች ምክንያት ታካሚዎች ለድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ከፍተኛ ቁጥር ባይኖራቸወም በመመረዝ ምክንያት የሚመጡ ታካሚዎች ስለመኖራቸው የገለጹ ሲሆን፤ "በምርመራ መሳሪያ እጥረት ምክንያት ታካሚዎች የምርመራ አገልግሎቱን ሌላ ቦታ እንዲፈልጉ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

አያይዘውም በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በስድስት ወራት ውስጥ ከ8 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ለምርመራ በሚያስልጉ መሳሪያዎች እጥረት ምክንያት የሕክምና አገልግሎትን ለመስጠት አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩን የገለጹም ሲሆን፤ በሆስፒታሉ ያሉ የምርመራ መሳሪያዎችና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር የተመጣጠነ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም አደጋዎች በሚኖሩበት ጊዜ ከተጠቀሰው አሃዛዊ ቁጥር ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ