የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በደረሰው የተገልጋይ ጥቆማ መሠረት የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አያለው እንዲሁም የነዋሪ መረጃ፣ ህትመት ስርጭት እና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ እጅጉ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው ግለሰቦቹ በጋራ በመመሳጠር ላለተገባ ሰው አገልግሎትን በገንዘብ ለመሸጥ በ10 ሺሕ ብር ተደራድረው የዲጂታል ምዝገባ በማከናወን ላይ ሳሉ በተደረገው ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ነው የገለጸው።

የተቋሙ የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ክፍል ከፖሊስ ጋር በመተባበር ላለፉት ሦስት የስራ ቀናት ክትትል ሲያደርግ በመቆየት ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2017 በጽ/ቤቱ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉንም አስታውቋል።

ተቋሙ በክትትሉ የተደራጁ የድምፅ ቅጂ እና ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለፖሊስ ማስረከቡንም ገልጿል።

ሕብረተሰቡም ከሕገ-ወጥ ደላሎች እና አገልግሎትን በገንዘብ ከሚሸጡ እራሱን እንዲጠብቅ ያሳሰበው ኤጀንሲው፤ መሰል ሁኔታዎች በአገልግሎቱ ላይ ሲገጥሙ በ7533 የነፃ የስልክ መስመር ማሳወቅ እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ